Sep 20, 2011

የመስቀል በዓል ክርስቲያናዊ አከባበር

/ አሉላ መብራቱ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ዘጠኙ የጌታችን ንዑሳን በዓላት አንዱ መስከረም 17 የሚከበረው የመስቀል በዓል ነው፡፡ መስቀል የሰላማችንና የድኅነታችን የመቀደሳችን አርማ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጆች ለማዳን፥የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት መስዋዕትነት የከፈለበት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበት መንበር፥ ሲሆን አምላካችንን የመንመለከትበት መስታወት ነው።
ይህ ዕለት 300 ዓመታት በላይ ጠፍቶ የነበረውን ቅዱስ መስቀል በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት መገኘቱን የምንዘክርበት በዚህም ደስ የምንሰኝበት ዕለት ነው፡፡ በዓሉ በምን ምክንያት እንደሚከበር ታሪኩን፣ በቅድሰት ቤተ ክርስቲያን ካህናቱና ምእመናን በአንድነት በመሆን እንዴት እንደሚያከብሩት፣ ምእመናን በየአካባቢያቸው በየቤታቸው እንዴት እንደሚያከብሩት ቀጥለን እንመልከት፡፡የቅዱስ መስቀሉ መዳፈን /መቀበር/ እና መገኘት
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ሕሙማንን በመፈወሱ ምክንያት በርካታ አሕዛብ ክርስቲያን እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ ይህን የተመለከቱ አይሁድ ቅዱስ መስቀሉን በአንድ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ እንዲቀበር አደረጉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥሉበት ቦታው ወደተራራነት ተቀየረ፡፡ ምንም እንኳን መስቀሉን ለማውጣት ባይችሉም በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ያውቁት ነበር፡፡ በሰባ ዓመተ ምሕረት በጥጦስ ወረራ ኢየሩሳሌም ስለጠፋች በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ፡፡ የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቅ ባለመገኘቱ መስቀሉ 300 ዓመታት በላይ ተዳፍኖ /ተቀብሮ/ ኖሯል፡፡
በ326 ዓ.ም. የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ቅዱስ መስቀሉን ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ አደረገች፡፡ እዚያም ደርሳ ጉብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍር መስቀሉ ያለበትን ቦታ ማግኘት አልቻለችም፤ ሰውም ብትጠይቅ የሚያውቅ አልተገኘም፡፡ በመጨረሻም የመስቀሉ መገኘት የእግዚአብሔር ፈቀድ ነበርና አንድ ይሁድ(ኪራዮስ) የተባለ አረጋዊ አግኝታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበትን አካባቢ አመለከታት፡፡ ይህ ሰው በኋላ በክርስቶስ አምኖ ተጠምቋል፤ ስሙም ኪራኮስ ተብሏል፡፡ ንግሥት ዕሌኒ ዕንጨት ደምራ በዚያ ላይ ዕጣን ጨምራ በእሳት ለኮሰችው፤ ቅዱስ ያሬድ በድጓው «ዘዕጣን አንጸረ ፣ሰገደ ጢስ» እንዳለ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል በማመልከቱ፡፡ ንግሥት ዕሌኒም ጢሱ ያረፈበት ቦታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበት እንደሆነ አመነች፡፡
በዚህም መሠረት ከመስከረም 17 ጀምሮ ሌሊትና ቀን የጉድፍን ኮረብታ ቆፍረው ካስወገዱ በኋላ ሦስት መስቀሎች የተገኙ ሲሆን፡፡ የጌታም መስቀል ሙት በማስነሣቱ ተለይቶ ታውቋል፡፡ መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ቀን 326 ዓ. ም. ነበር፡፡ ቅድስት ዕሌኒ ይህን ተአምር በማየቷ እጅግ ደስ አላት፡፡ ሕዝቡም ሁሉ መስቀሉን እየዳሰሱ ኪርያላይሶን እያሉም በመዘመር ደስታና ሐሴት አደረጉ፡፡ ቀኑ መሽቶ ጨለማ በሆነ ጊዜም የኢየሩሳሌም ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስና ንግሥት ዕሌኒ፣ ሠራዊቱና ሕዝቡ በሰልፍ በችቦ መብራት መዝሙር እየዘመሩ ቅዱስ መስቀሉን ወደ ቤተ ክርስቲያን ወስደው በአንድ የጸሎት ቤት አኖሩት፡፡ በኋላም ለመሰቀሉ መታሰቢያ ቤተክርስቲያን ተሰርቶ ተመርቆ የገባው /ቅዳሴ ቤቱ የተከበረው/ መስከረም 17 ቀን 326 ዓ. ም. ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ሁለቱም ዕለታት ይከበራሉ፤ በደማቅ ሁኔታና በመጀመሪያ ደረጃ የሚከበረው ግን መስከረም 17 ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት መጋቢት ዐሥር ቀን ሁልጊዜም በዐቢይ ጾም ወቅት የሚውል መሆኑና ለመስቀሉ የተሠራው ቤተ መቅደስ የከበረው መስከረም 17 መሆኑ ነው፡፡ ይህንንም ስንክሳር «የከበረ መሰቀልም ዳግመኛ የተገለጠበት መጋቢት ዐሥር ቀን ነው፡፡ ዜናውንም በዚሁ ቀን ጽፈናል፡፡ ምእመናንም በታላቁ ጾም መካከል በዓሉን ማክበር ስላልተቻላቸው በዓሉን ቤተ ክርስቲያኑ በከበረችበት ቀን አደረጉ፡፡ ይህም መስከረም 17 ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን አስቀድሞ ከከበረ መቃብር በንግሥት ዕሌኒ እጅ የተገለጠበት ነው» በማለት ያስረዳል፡፡
ቅዱስ መስቀሉ በተገኘበት ዘመን የምሥራች ዜና ከቦታ ወደ ቦታ የሚሸጋገረው እሳት በማንደድ ስለነበር በዘመኑ የነበሩ ክርስቲያኖች ደስታቸውን የገለጡት፣ የምሥራቹንም እስከ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ያደረሱት ችቦ በማብራትና መዝሙር በመዘመር ስለሆነ ይህን ለመዘከር በመሸ ጊዜ ሕዝበ ክርስተያኑ በየደጁ ችቦውን እያበራ ደስታውን ሲገልጥ እግዚአብሔርንም በመዝሙር ሲያመሰግኑ ያመሻሉ፡፡ ስንክሳሩ እንደሚገልጸው ክርስቲያን ሁሉ የትንሣኤውን በዓል በኢየሩሳሌም ተሰባስበው ያከብሩ እንደነበሩ ሁሉ የመስቀሉንም በዓል ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአንድነት ያከብሩ ነበር፡፡
በዓሉ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይከበራል?
ትልቁ የበዓል ማክበር ሥርዓት ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ በቤተ ክርስቲያን መሰባሰብ ነው፡፡ ሊቃውንቱ በፍትሐ ነገሥት «ተጋብኡ ኩሎ ዕለት ኀበ ቤተ ክርስቲያን ወፈድፋደሰ በዕለተ ሰንበት ወበበዓላት ወበዕለተ ትንሣኤ ዘውእቱ ዕለተ እሑድ፡፡ ወናሁ ንሬእዮሙ ለአሕዛብ ከመ ኢይዴኀሩ እምተጋብኦ በዕለተ በዓሎሙ፤ ሁልጊዜ በቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ፤ ይልቁንም በዕለተ እሑድ፣ በዕለተ ቀዳሚት፣ በጌታ በዓላት ወደ ቤተ ክርስቲያን ተሰብሰቡ፡፡ እንኳን ክርስቲያን አሕዛብም በዓል በሚያደርጉበት ቀን ከመሰብሰብ ወደኋላ እንዳይሉ እነሆ እናያቸዋለን፡፡» ያሉት ለዚህ ነው፡፡ /ፍትሐ ነገሥት ገጽ 254/ በዓሉን ማክበር የሚጀመረው በዋዜማው በመስከረም 16 ነው፡፡ ምእመናን ከየቤታቸው ዕንጨቱን ችቦውን ይዘው ለደመራ በተዘጋጀው ቦታ እያመጡ ይደምራሉ፡፡ ካህናቱ፣ ምእመናኑ ሁሉ በአንድነት ይሰበሰባሉ፡፡ ካህናቱም በደመራው ፊት ለፊት ጸሎት አድርሰው «መስቀል አብርሃ በከዋክብት አሰርገዎ ሰማየ እምኩሉሰ ፀሐየ አርአየ» እያሉ ደመራውን ይዞራሉ ትርጉሙም «መስቀል በክዋክብት አበራ፤ ሰማይን አስጌጠ፤ከሁሉም በላይ ፀሐይን አሳየ» ማለት ነው፡፡ በገጠር ሕዝቡ ችቦውን በማብራት «ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ» እያለ ደስታውን ይገልጣል፡፡ በከተማ አካባቢ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ስለ መስቀል የተዘመሩ መዝሙራትን በመዘመር እግዚአብሐርን ያመሰግናሉ፡፡
በገጠሩ የሀገራችን ክፍል ደመራው የሚለኮሰው በ17 ጠዋት ሲሆን በአዲስ አበባና በአካባቢው ግን ደመራው የሚለኮሰው ጸሎቱ እንዳለቀ ነው፡፡ ደመራው የተጸለየበትና የተባረከ ስለሆነ ሕዝቡ አመዱንና ትርኳሹን እየተሻማ ወደየቤቱ ይዛ ይሄዳል፡፡ አመዱን ቢቀቡት፣ ቢተሻሹት፣ በጥብጠው ቢጠጡት ይፈውሳል፤ ለከብት እንኳን ሳይቀር መድኃኒት ይሆናል፡፡ ባላገሩ ከብቱን ሁሉ በትርኳሹ ይተኩሳል ጤና እንዲሆንለት፡፡ የበዓሉ ዕለት ምእመናን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው የነግህ ጸሎት ያደርሳሉ፡፡ በዓላት በዚህ ምድር ሳለን ተድላ ነፍስ ተድላ ሥጋ ያለባትን፣ ፍጹም የሆነ ሰላም፣ ረፍት፣ ደስታ የምትሰጠውን መንግስተ ሰማያትን መቅመሻ ናቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን ከምትፈጽምባቸው ሕይወቶቿ ዋናው ቅዳሴ ነው፡፡ ስለዚህ ምእመናን በዚህ ዕለት ቅዳሴ አስቀድሰው ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለው ደስ ብሏቸው በዓሉን ያከብሩታል፡፡ በዕለቱ የሚቀደሰው ቅዳሴ ስለ ነገር መስቀል አብዝቶ የሚናገረው ቅዳሴ ዘዮሐንስ አፈወረቅ ነው፡፡ በዚህ ቅዳሴ ከሚነበበው የነገረ መስቀል ንባብ መካከል ለመጥቀስ ያህል፦ «ኦ አዕዳው እለ ለሐኳሁ ለአዳም ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል፤ ኦ አእጋር እለ አንሶሰዋ ውስተ ገነት ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል፤ ኦ አፍ ዘነፍሐ ውስተ ገጹ ለአዳም መንፈስ ሕይወት ብሒዐ መጺጸ ዘምስለ ሐሞት ሰረበ፤አይ አፍ ወአይ ከናፍር ወአይ ልሳን ዘይትናገር ሕማማቲሁ ለወልድ፤ ልብ ይትከፈል ፣ወሕሊና ይዘበጥ ፣ወነፍስ ትርዕድ፣ ወሥጋ ይደክም ሶበ ይትነገር ሕማማቲሁ ለፍቁር፤አዳምን የፈጠሩ እጆች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ፣ ወዮ፤ በገነት የተመላለሱ እግሮች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ፣ ወዮ፤ በአዳም ፊት የሕይወት መንፈስን እፍ ያለ አፍ ከሐሞት ጋራ የተቀላቀለ መጻጻን ጠጣ፣ ወዮ፤ የወልድን መከራውን የሚናገር ምን አፍ ነው፣ ምን ከንፈር ነው፤ ምን አንደበት ነው፤የፍቁር የጌታ ሕማማት በተነገረ ጊዜ ልብ ይለያል፤ ሕሊናም ይመታል፤ ነፍስም ትንቀጠቀጣለች፤ ሥጋም ይደክማል፣ /ቅዳሴ ዮሐንስ አፈወረቅ/ በዋዜማው /በደመራ ዕለት/፣ በዕለቱ በጸሎተ ነግህ እና በጸሎተ ቅዳሴ የሚሰበኩት ምስባካት የሚከተሉት ናቸው፡፡
ወረከብናሁ ውስተ ፆመ ገዳም፡፡ ንበውዕ እንከሰ ውስተ አብያቲሁ ለእግዚአብሔር፡፡ ወንሰግድ ውስተ መካን ኀበ ቆመ እግረ እግዚእነ፡፡ በዱር ውስጥም አገኘነው፤ ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን፤ እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን» /መዝ. 1316/ «ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ፤ ከመ ያምሥጡ እሞገጸ ቅስት፤ ወይድኀኑ ፍቁራኒከ ፤ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፤ ወዳጆችህ እንዲድኑ» /መዝ. 594/   የሚነበቡት የወንጌልና የመልእክታት ክፍሎችም /ዮሐ. 1925-28 ዮሐ. 314-22፣ ማቴ. 816-28፣ ሐዋ. 526-33 1ኛ ጢሞ. 59-16፣ያዕ 3፡11/ ፍጻሜ ናቸው፡፡
ቅዳሴው፣ መዝሙራቱ፣ ምንባባቱ ስለ ቅዱስ መስቀል በርካታ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ እነዚህንም ነገሮች ቅዱስ ያሬድ «መስቀል በኩል ጊዜ፣ ወለኩሉ ሰዓት፤ መስቀል በጊዜው ሁሉና በሰዓቱ ሁሉ ነው» እንዳለው ስለ ቅዱስ መስቀል ዘወትር ስናስብ በተለይም ይህን በዓል ስናከብር እነዚህን ነገሮች እያሰብን ደስ ልንሰኝ እግዚአብሔርንም ልናመሰግን ይገባል፡
መስቀል ብርሃን ነው
ጨለማ የተባለ ኃጢአትና ሞት በሞትም ላይ ሥልጣን ያለው የጨለማው አበጋዝ ዲያብሎስ ድል የተነሳበት፤ ሥልጣኑ የተሻረበት በመሆኑ መስቀል ብርሃን ተብሏል፡፡ በጌታችን የመስቀል ሞት ብርሃን የተባለውን ሰማያዊ ሕይወት አግኝተናል፡፡ «ሕይወትም በእርሱ ነበረ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበር፤ ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም አላሸነፈውም፡፡» እንዲል፡፡ /ዮሐ. 14-5/
ከዚህ በተጨማሪ የመስቀል ብርሃን መባል ከበዓሉ ጋር የተያያዘ ታሪካዊ ይዘትም አለው፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ከመክስምያኖስ ጋር በተዋጋ ጊዜ በሰማይ በፀሐዩ ብርሃን ላይ «በዚህ የመስቀል ምልክት ጠላትህን ድል ታደርጋለህ» የሚል የመስቀል ምልክት አየ፡፡ የመስቀል ምልክትን በፈረሱና በበቅሎ ልጓም፣ በጦር መሣሪያውና በጦር ልብሱ፣ በባንዲራው ላይ አድርጐ ጠላቱን አሸንፏል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ይህን ታሪክ መሠረት አድርጋ «መስቀል አብርሃ በከዋክብት አሰርገው ሰማየ እምኩሉሰ ፀሐየ አርአያ» እያለች ትዘምራለች፡፡ በሌላም በኩል ቅዱስ መስቀል ከተዳፈነበት ቦታ መገኘቱና መታየቱ «መስቀል አበራ» አስብሎታል፡፡ ምክንያቱም ጨለማ መሰወር ፤ብርሃን ደግሞ መገለጥ ነውና፡፡
መስቀል የድኅነት፣ የሰላም ምልክት ነው፡፡
ጌታችን የፈጸማቸው የማዳን ሥራዎች ሁሉ ፍጻሜ መስቀል ነው፡፡ ራሱ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ «ሁሉ ተፈጸመ» ብሏል፡፡ /ዮሐ. 19፡30/ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ «መስቀል መልዕልተ ኩሉ ነገር፤ ያድኅነነ እምፀር መስቀል ከሁሉ በላይ ነው፤ ከጠላት /ዲያብሎስ/ ያድነናል»፣ «አድኀነ ሕዝቦ በመስቀሉ፣ ሕዝቡን በመስቀሉ አዳነ» በማለት ዘምሯል፡፡ ዲያብሎስ የመስቀል ምልክትን ይፈራል፤ በመስቀል ፊት መቆም አይችልም፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በጦር ሠራዊቱና በጦር መሣሪያዎቹ ሁሉ ላይ የመስቀል ምልክት አድርጎ በመክስምያኖስ ላይ ያደረ ርኩስ መንፈስን በማራቁ አላዊውን ንጉሥ በቀላሉ መሸነፍ ችሏል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ክርስቲያን ነገሥታት በዘውዳቸው ላይ፣ በጦር መሣሪያዎቻቸው ላይ የመስቀሉን ምልክት ይጠቀሙበታል፡፡ ምእመናን የመስቀል ምልክትን በሰውነታቸው ላይ በተለያየ ቦታ ይነቀሱታል፤ ልቡናቸውን ይባርክ ዘንድ በደረታቸው ላይ ያንጠለጥለታል፤ በደነገጡ፣ የሕሊና ሰላም ባጡ ጊዜ ቅዱስ ያሬድ «መስቀል ትእምርተ ሰላምነ፤ መስቀል የሰላማችን ምልክት ነው፡፡» እንዳለ በትእምርተ መስቀል አማትበው የሰላም ፀር የሆነውን ዲያብሎስን ያርቁበታል፡፡ ታዲያ ይህ የሚሆነው፣ ትእምርተ መስቀል የተሰጠው እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ለወዳጆቹ ነው እንጂ እንዲያው ዝም ብለው ለጌጥ ለሚያንጠለጥሉት አይደለም፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ «ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ፤ ከመ ያምሥጡ እምገጸ ቅስት፤ ወይድኀኑ ፍቁራኒከ፡፡ ለሚፈሩህ ምልክትን /መስቀል/ ሰጠሃቸው ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፡፡ ወዳጆችህም እንዲድኑ፡፡» እንዳለ፡፡ /መዝ. 594-5/ ለሚፈሩህና ለመዳጆችህ አለ እንጂ ለሁሉም አላለም፡፡ ስለዚህ ዘወትር በጸሎታችን «መስቀል ኃይልነ፣ መስቀል ጽንዕነ፣ መስቀል ቤዛነ፣ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ፡፡ አይሁድ ክሕዱ ንሕነሰ አመነ ወእለ አመነ በኃይለ መሰቀሉ ድኅነ፡፡» እንላለን፡፡ በእያንዳንዷ ዕለታዊ ሕይወታችን፡፡
የመስቀል ምልክትን እንጠቀማለን፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ከጉልላቷ በላይ መስቀል ታደርጋለች፤ በቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎች በርና መስኮት ላይም የመስቀል ምልክት ታደርጋለች፡፡ እነዚህ ነገሮች አሁን የመጡ ሳይሆን ሐዋርያት «እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፡፡» ፣ «ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክሕት ከእኔ ይራቅ» /1 ቆሮ. 1፡23፣ገላ. 6፡14/ እያሉ መስቀል የሞት ምልክት ሳይሆን የድኅነት ምልክት መሆኑን ካስተማሩ በኋላ የተጀመረ ነው፡፡ ከሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ እስከ ሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የኖረው ጠረጡለስ በዘመኑ ክርስቲያኖች በመስቀል እንዴት ይጠቀሙ እንደ ነበር የሚከተለውን ተናግሮአል፡፡ «በተግባራችን ሁሉ በምንገባበትና በምንወጣበት ጊዜ፣ ልብሶቻችንን  ከመልበሳችን በፊት፣ ከመታጠባችን በፊት፣ በቀንና በማታ ወደ ምግብ ገበታ በምንቀርብበት ጊዜ፣ ማታ መብራታችንን በምናበራበት ጊዜ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ በምንጀምርበትና በምንፈጽምበት ጊዜ፣ በዕለታዊ ሕይወታችን መደበኛ ሥራችንን በምንጀምርበት ጊዜ በትእምርተ መስቀል ፊታችንን እና መላ ሰውነታችንን እናማትባለን፡፡»
መስቀል አንድ የሆንበት ነው
ቅዱስ ጳውሎስ «እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረስ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በእርሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእረሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፡፡ መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና፡፡» /ኤፌ. 214-18/ ብሎ እንዳስተማረ በቅዱስ መስቀል እግዚአብሔርና ሰው ታርቀዋል፤ ህዝብና አህዛብ አንድ ሆነዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን ሰብስባ በጸሎት፣ በመዝሙር ይልቁንም የአንድነት መገለጫ በሆነው በጸሎተ ቅዳሴ ታከብረዋለች፡፡ ምእመናንም በአንድነት ሆነው አብረው በመብላት ፤አብረው በመጠጣት በዓሉን ያከብሩታል፡፡ ምግበሥጋ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ በልተን ጠጥተን በሕይወት እንድንኖር እግዚአብሔርንም እንድናመሰግን አምላካችን መብልና መጠጥን ሕይወት አድርጎ ሰጥቶናል፡፡ በበዓላትም ተድላ ሥጋ ማድረግ የተገባ ስለሆነ ምእመናን አብሮ በመብላትና በመጠጣት ያከብሩታል፡፡ ይህ ሲባል ግን አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት ከእግዚአብሔር ተለይቶ የሥጋን መሻት፤ የዓይንን አምሮት ለመፈጸም እስክንደርስ መሆን የለበትም፡፡ ይልቁንም የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት መንፈሳዊ ደስታን በመደሰት በዓሉን ማሳለፍ ይገባናል፡፡
ማጠቃለያ
ስለ ቅዱስ መስቀል እነዚህን ለምሣሌ ያህል ጠቀስን እንጂ የነገረ መስቀል ትምህርት በዚህ የሚወሰን አይደለም፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የዘመን አቆጣጠር ከመስከረም 17-25 ያለው ጊዜ ዘመነ መስቀል ይባላል፡፡ በዚህ ጊዜ ነገረ መስቀል ይነገራል፤ መዝሙረ መስቀል ይዘምራል፡፡ ምእመናን በዚህ ጊዜ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመገኘት ነገረ መስቀሉን ልንሰማ እግዚአብሔርንም በመዝሙር ልናመሰግን ይገባል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አንዱ የነበሩት መጋቤ ብሉይ ሠይፈ ሥላሴ ዮሐንስ ስለ ቅዱስ መስቀል ያስተማሩትን ትምህርት ጠቅሰን ጽሑፋችንን እናጠቃልላለን፡፡ «ቅዱስ መስቀል በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ሁሉ በሁሉ ነው፡፡ ቅዱስ መስቀል የወንጌል መሠረትና ልብ ነው፡፡ ቅዱስ መስቀል በቤተ ክርስቲያን ከቀረ የወንጌል ፍሬ ነገር ቀረ ማለት ነው፡፡ የመስቀሉ ነገር በብዙዎች ዘንድ የጥበብ ተቃራኒ የሆነ ሞኝነትን መስሎ መሰናክል ሆኗል፡፡ ለሚያምኑት ግን የእግዚአብሔር ኀይልና ጥበብ ነው፡፡ ዓለም በጥበቡና በዕውቀቱ፣ በኀይሉም አልዳነም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የዓለምን ኀይል፣ ጥበብና ዕውቀት ሞኝነት በመሰለው በመስቀል ነገር ከንቱ አድርጎታል፡፡ ስለሆነም በድካምና በሞኝነት ማለት በመስቀል ስብከትና በእምነት ዓለምን ለማዳን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኗል፡፡ ስለ መስቀልና በመስቀል ስለተሰቀለው ክርስቶስ መሰበክ በማያምኑት ዘንድ ሞኝነት፣ ድካምና መሰናክል ቢመስልም በምእመናን ዘንድ ግን የእግዚአብሔር ኀይል ሆኖ ይታያል፡፡ ምክንያቱም በሰው ዘንድ ሞኝነት ሆኖ የታየው የእግዚአብሔር ሥራ ከሰው ጥበብ ይልቅ ስለሚጠበብ ነው፡፡ በሰው ዘንድ ድካም ሆኖ የታየው የእግዚአብሔር ሥራም ከሰው ኀይል ይልቅ ስለሚበረታ ነው፡፡ እንግዲህ ቅዱስ መስቀል በሚያምኑና በማያምኑ መካከል መለያ ምልክት ነው፤ መለኪያ ሚዛንም ነው፡፡ ለእኛ ለምናምን ቅዱስ መስቀል ወደ ሰማይ የምንደርስበት መሰላል ነው፡፡ ለማያምኑ ግን ወደ ሰማይ እንዳይደርሱ የሚሰናከሉበት እንቅፋት ነው፡፡ በክርስቶስ አምናለሁ የሚል ሁሉ እንደ አይሁድ «መስቀሉን አይግፉ» ነገር ግን እንደ ቅድስት ዕሌኒ መስቀሉን ይፈልግ፤ መስቀል ከሁሉ ነገር በላይ ነውና፡፡»
ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

1 comments:

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።