Oct 14, 2011

ወዳጄ ሆይ ተነሽ፣ ውበቴ ሆይ ነይ


ምንጭ፦ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል
ብዙውን ጊዜ ጠቢቡ የሚለው ቃል ይቀጸልለታል። በእርግጥም በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ንጉሥ ሆኖ በተሾመ ጊዜ በፍጹም አትኅቶ (ራስን ዝቅ በማድረግ) መልካሙንና ክፉውን ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡናን ስጠው በማለት ከብርና ከወርቅ ይልቅ የበለጠውን ነገር በመለመኑ እግዚአብሔር ተደሰተበት። እኔ እንደቃልህ አድርጌልሀለሁ እነሆ ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ ከአንተም በኋላ እንዳይነሳ አድርጌ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሀለሁ ተባለ። / ነገ. ፫፥፱-፲፬/ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከ፲፻፲፱-፱፻፸፱ .. የነገሠው ሰሎሞን። 
ሰሎሞን እጅግ በጣም በጥበብና ልብን በሚነኩ ምሳሌዎች የተሞሉ አምስት መጻሕፍትን ደርሷል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ይባላል። ከመዝሙራት ሁሉ የሚበልጥ መዝሙር እንደማለት ነው። በዚህ መጽሐፍ እግዚአብሔር አምላካችን በገለጠለት መጠን በሴት አንቀጽ እየጠራና በፍቅር እየመሰለ ስለሐዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያንና ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ብዙ ምሥጢር ተናግሮበታል።

ስለድንግልናዋ እኅቴ ሙሽራ የተቆለፈ ገነት፣ የተዘጋ ምንጭ፣ የታተመ ፈሳሽ ናት። /መኃ. ፬፥፲፪/ ስለስደቷ ደግሞ አንቺ ሱለማጢስ ሆይ ተመለሽ፣ ተመልሽ፣ እናይሽ ዘንድ ተመለሽ፣ ተመለሽ። ይላታል /መኃ. ፯፥፩/ በዚያም ሳያበቃ ስለእረፍቷና ትንሣኤዋ ደግሞ ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፤ ወዳጄ ሆይ ተነሽ፣ ውበቴ ሆይ ነይ። በማለት ይናገራል /መኃ. ፪፥፲/ ይህንን ቃል ግዕዙ እንዲህ ይለዋል ያውሥእ ወልድ እኁየ ወይብለኒ ተንሥኢ ርግብየ ወንዒ ሠናይትየ። ልጅ ወንድሜ ወልድ /እግዚአብሔር/ እንዲህ አለኝ። ወዳጄ /ርግቤ/ ሆይ ተነሽ፣ ውበቴ ሆይ ነይ። ውዴ የተባለ ወልድ፤ የአብ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድያ ልጁ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው እንዳለ /ማቴ. ፫፥፲፯/
ወዳጄ፣ ውበቴ የተባለች ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። የሰው ልጅ በሰይጣን አሽክላ ተተብትቦ በነበረበት የጨለማ ዘመን ለሰው ልጆች ብርሃን ክርስቶስን ያስገኘች በመሆኗ እንደዚሁም ቅድመ ዓለም ያለ እናት የተወለደ ቃለ አብ፤ ድኅረ ዓለም ያለ አባት ሲወለድ ለእናትነት የተመረጠች፣ ስደቱን የተሰደደች፣ በአጠቃላይ በመዋዕለ ሥጋዌው ከአጠገቡ ያልተለየች በመሆኗ ወዳጄ ይላታል።  ውበቴ መባሏም ስለብዙ ምክንያት ነው። አስቀድሞ አባቷ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ ልጄ ሆይ ስሚ፣ እይ፣ ጆሮሽንም አዘንብይ፣ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ ንጉሥ ውበትሽን ወድዷልና እርሱ ጌታሽ ነውና። በማለት እንደተናገረ /መዝ. ፵፬፥፲/ እመቤታችን በውስጥ በአፍአ፣ በነቢብ በገቢር፣ ፍጹም እንከን የሌለባት፤ ድንጋሌ ሥጋን ከድንጋሌ ነፍስ አስተባብራ የተገኘች፤ በነፍስ፣ በሥጋ፣ በልቡና ንጽሕት፣ ቅድስት በመሆኗ ነው። ቅዱስ ኤፍሬም በረቡዕ ውዳሴው ላይ አብ በሰማይ አይቶ እንደ አንቺ ያለ አላገኘምና፤ አንድ ልጁን ላከው፣ በአንቺም ሰው ሆነ። በማለቱ አንስት በሙሉ መርገመ ሔዋን ይተላለፍባቸው ነበርና ለአምላክ እናት የምትሆን ሴት በጠፋችበት እርሷ መገኝቷን ያመለክታል። በተመሳሳይ መልኩም ይህን ሃሳብ ሊቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው እንዲህ በማለት ያጠነክረዋል። እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ ምሥራቅንና ምዕራብን፣ ሰሜንና ደቡብን፣ ዳርቻዎችንም በእውነት ተመለከተ፤ ተነፈሰ፣ አሻተተም እንደ አንቺ ያለ አላገኘም፤ የአንቺን መዐዛ ወደደ የሚወደውን ልጁን ወደ አንቺ ላከ። እንግዲህ እመቤታችን ውበቴ መባሏ በእንደዚህ ያለው ምክንያት መሆኑን ማወቅ ይገባል።
እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ሦስት ዓመት ከቤተሰቧ ጋር፣ አሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀናት ጌታን ጸንሳ፣ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ጋር፣ አሥራ አምስት ዓመት በወንጌላዊው ዮሐንስ ቤት ከኖረች በኋላ በስድሳ አራት ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን በ፵፱ .. አርፋለች። /ነገረ ማርያም/ የሰማዕታት እናታቸው፣ የሐዋርያት ሞገሳቸው፣ የነቢያት ትንቢታቸው፣ እግዝእተ ብዙኃን ድንግል ማርያም፤ አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ኃይል አርያማዊት /ከሰማይ የወረደች ኃይል/ አይደለችም። ሰው ሆና ከአዳም ዘር የተወለደች እንጂ። ለዚህም ልደቷና እድገቷ ብቻ ሳይሆን እረፍቷም አሳማኝ ምስክር ነው። ነገር ግን የጌታችን እናቱ፤ ከፍጡራን በላይ የተባለች ንግሥት፤ ሰማይና ምድር የማይችሉትን አምላክ በማኅፀኗ የተሸከመች እመቤት፤ አጥብታ ያሳደገች፣ አዝላ የተሰደደች፣ በእግረ መስቀሉ ቆማ ያለቀሰች እናት፤ ሥጋዋ መፍረስ መበስበስን ያይ ዘንድ ወይም እንደሌላው ሰው እስከ ትንሣኤ ዘጉባኤ በመቃብር ይቆይ ዘንድ አይገባምና ተነሣች።የእመቤታችን ትንሣኤ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ የተደረገ ሳይሆን በቅዱስ መጻሕፍት በትንቢት የተገለጸ ነበር። ቅዱስ ዳዊት ተንሥእ እግዚኦ ውስተ እረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ። አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦትም። ይላል /መዝ. ፻፴፩፥፰/ ነቢዩ ይህንን ቃል የተናገረው ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰምያት የመቅደስህ ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነስ ሲል ነው። ታቦት የጽላት ማደሪያ እንደሆነ ሁሉ እመቤታችንም ለክርስቶስ ማደሪያ በመሆኗ ታቦት ትባላለች።
ሌላው በመግቢያችን የገለጽነው የጠቢቡ ሰሎሞን ቃል ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛነቱን ከፈጸመ በኋላ ወደቀደመ ክብሩ እንደተመለሰ ሁሉ እመቤታችንም የክርስትናን ፍሬ ማፍራት ከአየች በኋላ በቀኙ ትቀመጥ ዘንድ ተነሽ ነይ ብሏቷል። ዳዊትም በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች እንዳለ። /መዝ. ፵፬፥፱፣ ኢሳ. ፷፥፩/ የእመቤታችን ትንሣኤ ምንም እንኳ በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ የተደረገ ቢሆንም መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዝ ፍቱልኝ፣ ድንጋይ ፈንቅሉልኝ ያልተባለበትና በሦስተኛው ቀን የተፈጸመ በመሆኑ ከጌታ ትንሣኤ ጋር ይነፃፀራል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን የቅዱሳንን ታሪክ እንናገራለን። ያቺ ዋጋው የላቀ ሽቱ በራሱ ላይ ያፈሰሰች ሴት /ማርያም ባለሽቱዋ/ ደቀመዛሙርቱ በተቃወሙ ጊዜ ከገሰጻቸው በኋላ እውነት እላችኋለሁ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ሥፍራ በሚሰበክበት እርሷ ያደረገችው ደግሞ ለእርሷ መታሰቢያ እንደሆነ ይነገራል። እንዳለ /ማቴ. ፳፮፥፲፫/ የቅዱሳንን ሥራ ያከበረ ጌታ የእናቱንማ እንዴት? እመቤታችንም ብእሲተ ዘካርያስ ኤልሳቤጥን በጎበኘች ጊዜ እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል። በማለት እንደተናገረች /ሉቃ. ፩፥፵፰/ ልደቷን፣ እድገቷን፣ መጽነስ መውለዷን፣ እረፍቷን፣ መነሳቷን መዘከር፣ መመስከር በረከትን እንደሚያስገኝ ልብ ይሏል።
የእመቤታችንን የመጀመሪያ ትንሣኤ ያየው ትንሣኤ ሙታን የለም ከሚሉት ከሰዱቃውያን ወገን የተጠራው ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ ነበር። ቶማስ ሀገረ ስብከቱ ሕንድ ነው። በዚያ ሲያስተምር ሰንብቶ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችንን ስታርግ ያገኛታል። ትንሣኤዋን ከእርሱ ሰውራ ያደረገች መስሎት አዘነ።ፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ እንዲል ነገረ ማርያም፤ ከደመናው ተወርውሮ ሊወድቅ አሰበ። እርሷ ግን እርገቷን ያየ እርሱ ብቻ እንደሆነና ለሌሎችም እንዲነግራአቸው ለምልክትም እንዲሆን ሰበኗን /መግነዟን/ ሰጠችው። እርሱም ሐዋርያትን የእመቤታችን ነገርስ እንደምን ሆነ? ቢላቸው አግኝተን ቀበርናት አሉት። ቶማስም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል? አላቸው። ሊያሳዩትም ፈልገው መቃብሯን ቢከፍቱ ባዶ ሆኖ አገኙት። እርሱ ግን አታምኑኝም ብዬ እንጂ እርሷስ ተንሥታ አርጋለች በማለት ሰበኗን አሳያቸው። ለበረከትም ይሆን ዘንድ ተከፋፍለው ወደየሀገረ ስብከታቸው ሔዱ። ዛሬ በቅዳሴ ጊዜ ሠራኢው ዲያቆን በሚይዘው የመጾር መስቀል ላይ በሁለት ጆሮዎች /ቀዳዳዎች/ አልፎ በእንጨት ላይ ተጠምጥሞ የምናየው መቀነት መሰል ጨርቅ የዚያ ሰበን ምሳሌ ነው።
አንዲት ቅድስት ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያናችን በቀኖናዋ ወስና ከነሐሴ -፲፭ ያሉትን ቀናት በአዋጅ የምትጾምበት ምክንያትም እንደሚከተለው ነው። እመቤታችን በአረፈች ጊዜ ሐዋርያት ቅዱስ ሥጋዋን ያሳርፉ ዘንድ ወደ ጌቴሴማኒ የመቃብር ቦታ ሲወስዷት ልማደኞች አይሁድ ተነሱባቸው ቀድሞ ልጇን ሞተ፣ ተነሣ፣ አረገ እያሉ ሲያሳድሙ ኖሩ። ዛሬ እሷንም እንዲሁ ሊያደርጉ አይደለምን በማለት ያቃጥሏት ዘንድ ተማከሩ። ታውፋንያ የተባለ የጎበዝ አለቃ ቀድሞ ደርሶ የአልጋውን ሸንኮር በመያዝ ከመሬት ሊጥላት ሲሞክር መልአከ እግዚአብሔር ደርሶ ሁለት እጆቹን በሰይፍ ቆርጦ ሥጋዋን ከዮሐንስ ጋር ወደ ገነት አሳረገ። በዚያም በዕፀ ሕይወት ዛፍ ሥር አስቀምጧት ጻድቃን ሰማዕታት ሲዘምሩላት፣ እነዳዊት በበገና፣ እነዕዝራ በመሰንቆ ሲያመሰግኗት ቆዩ። ሐዋርያትም ሥጋዋን አግኝተው ይቀብሯት ዘንድ ከነሐሴ ጀምሮ እስከ ፲፬ ሁለት ሱባኤ ያዙ። በ፲፬ኛው ቀን ጌታ ሥጋዋን ሰጥቷቸው በፍጹም ደስታ በጌቴሴማኒ አሳረፏት። በሦስተኛውም ቀን ተነሥታ ስታርግ ቶማስ ተመለከታት።
እንግዲህ የእመቤታችንን ትንሣኤ ከቶማስ በቀር ሌሎች አላዩም ነበርና በዓመቱ ከያሉበት ተሰባስበው ጾም ጸሎት ጀመሩ። የለመኑትን የማይነሳ፣ የነገሩትን የማይረሳ አምላካችንም መላውን ሐዋርያት ወደ ገነት አውጥቶ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረው መቃብር እመቤታችንን ነፍስዋን ከሥጋዋ አዋሕዶ አንሥቶ፣ ትንሣኤዋንና እርገቷን አሳይቶ፣ ለዓለም ይህንን እንዲያስተምሩ አዘዛቸው። ከዚያን ጊዜ በኋላ የተነሱ አበውና እኛም በሥጋ ዓይናችንም ባይሆን በመንፈሳዊ ዓይናችን ትንሣኤዋን እናይ ዘንድ፣ በረከቷን ረድኤቷን አሳድራብን ከልጇ ከወዳጇ ምሕረትን ይቅርታን ትለምንልን ዘንድ፣ ጾመን ጸልየን ትንሣኤዋን በፍጹም ደስታ እናከብራለን። ጾም ጥሬ ቃሉ መከልከል፣ ለተወሰነ ጊዜ ከምግብ፣ ከመጠጥ ወዘተ መታቀብ ማለት ነው። ጾም ደማዊት ነፍስን ለነባቢት ነፍስ የምታስገዛ ደገኛ ሥርዓት ነች። አዳም ከአምላኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው ትእዛዝ አትብላ የሚል ነበር። ይህም የፈጣሪነትና የፍጡርነት መለያ፣ ጾምንም ማስተማሪያ ነው። ይህ ትእዛዝ በመጣሱም ሞት ወደ ዓለም ገብቷል። ጾም ወደ እግዚአብሔር ያቀርባል። /ኢዩ. ፩፥፲፬፣ ፪፥፲፪/ ጾም እግዚአብሔርን ለመለመንና በረከትን ለመቀበል ያስችላል። /ዮና. ፫፥፰-፲፣ ዳን. ፱፥፭-/
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ፴ ዓመቱ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከተጠመቀ በኋላ ለማስተማር ከመውጣቱ በፊት ወደገዳመ ቆሮንቶስ በመሔድ መዓልትና ሌሊት ጾሟል። /ማቴ. ፬፥፪/ ይህንንም አብነት አድርገው ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ በመላው ዓለም ለስብከት ከመሰማራታቸው በፊት ጾመ ሐዋርያት ተብሎ የተሰየመውን ጾመዋል።ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዮስ መልእክቱ በቀረውስ ወንድሞች ሆይ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ በጎነት ቢሆን ምሥጋና ቢሆን እነዚህን አስቡ ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል በማለት እንዳስተማረን /ፊል. ፬፥፱/ የአባቶቻችንን አሠረ ፍኖት በመከተል በሕገ እግዚአብሔር በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እንጓዛለን።
ለጻድቃን ለሰማዕታት ለሐዋርያት ለነቢያት የተለመነች እናታችን ለእኛም ትለመነን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።