Aug 29, 2017

አቡነ ተክለ ሃይማኖት እረፍት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †
እንኳን ለአባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት የእረፍት ቀን በሰላም አደረሳችሁ
በረከታቸው ይድረሰን
ስንክሳር ዘወርኀ ነሐሴ ፳፬†

 አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመምፈስ ቅዱስ ስም ነሐሴ ሃያ አራት በዚች ቀን የክርስቶስ ምስክሩና ሐዋርያው የሆነ የመርዓስ ኤጲስቆጶስ ተጋዳይ ቅዱስ አባት ቶማስ አረፈ። የዚህንም አባት ትሩፋቱንና ገድሉን ሰው ተናግሮ ሊፈጽመው አይችልም እርሱ አስቀድሞ በጾም በጸሎት በስጊድ ቀንና ሌሊትም በመትጋት ለድኆችና ለምስኪኖችም በመራራት  ተጠምዶ የሚኖር ነው።
ከዚህም በኋላ መርዓስ ለሚባል አገር ኤጲስቆጶስ ይሆን ዘንድ የክብር ባለቤት ጌታችን መረጠው መንጋውንም እንደ ሐዋርያት ጠበቀ። ከሀዲ ዲዮቅልጥያኖስም በነገሠ ጊዜ ክርስቲያኖችን ያሠቃያቸው ዘንድ ከመኳንቶቹ ።  አንዱ ወደዚያች አገር ደረሰ እርሱም ቅዱስ ቶማስን ወደርሱ ያቀርቡት ዘንድ ጭፍሮቹን ላከ እነርሱም እየደበደቡ በምድር ላይ እየጐተቱ ወሰዱት ደሙም እንደ ውኃ ፈሰሰ።ከዚህም በኋላ መኰንኑ ቅዱስ ቶማስን ለአማልክት ስገድ አለው ቅዱሱም እንዲህ ብሎ መለሰለት እኔ ከሕያው እግዚአብሔር ልጅ ከጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ለረከሱ ጣዖታት አልሰግድም ለረከሱ ጣዖታት የሚሰግድ  ሁሉ የተረገመ ነውና።መኰንኑም ተቆጥቶ እጅግ የበዛና ዕፁብ ድንቅ የሆነ ሥቃይን አሠቃየው የነዳጅ ድፍድፍን አፍልተው በላዩ በአፉና በአፍንጫው ውስጥ ጨመሩ እንዲህም እያደረጉበት እስከ ብዙ ዘመናት ኖረ።

የእሊህ ከሀድያን ልባቸው እንደ ድንጊያ የጸና ስለሆነ ቅዱስ ቶማስ ቶሎ እንዲሞት አልፈለጉም። ሌሎች ብዙዎች ሰዎችን ያሰፈሩአቸው ዘንድ የክብር ባለቤት ክርስቶስንም ይክዱት ዘንድ የሥቃዩን ዘመን አስረዘሙ እንጂ።እርሱ የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል የጸና ነውና ማሠቃየቱን ከሀድያን በተቸነፉ ጊዜ ስለ ስሕተታቸውም ይዘልፋቸው ስለነበር ስለዚህ በጨለማ ቦታ ጣሉት በዚያም ሃያ ሁለት ዓመት ኖረ።ከሀድያንም በየዓመቱ ወደርሱ ገብተው ከሕዋሳቱ አንዱን ይቆርጣሉ።በዚያም ቦታ አፍንጫውን ከንፈሮቹን ጆሮዎቹን እጆቹንና እግሮቹን ቆረጡ መንጋዎቹም ያረፈ መስሏቸው በየዓመቱ መታሰቢያውን ሲያደርጉ ኖሩ ።ነገር ግን አንዲት ክርስቲያናዊት ሴት በጣሉት ጊዜ ስለአየችው ቦታውን ታውቅ ነበር እርሷ በሌሊት ወደርሱ ተሠውራ በመሔድ ትመግበዋለች ።ጻድቅ ቁስጠንጢኖስም እስከ ነገሠና የቀናች የክርስቶስን ሃይማኖት ክብር እስከ ገለጠ ድረስ እንዲህ ሲሠቃይ ኖረ።

ይህም  ንጉሥ ክርስቶስን በመታመን የታሠሩ እሥረኞችን ሁሉ በሀገሮች ሁሉ በወህኒ ቤት ያሉትን ይፈቷቸው ዘንድ አዘዘ።
ይችም ሴት ሒዳ ስለ ቅዱስ ቶማስ ከእርሱ የሆነውን ሃያ ሁለት ዓመት ተጥሎ እንደኖረ ለካህናቱ ነገረቻቸው በውስጡ ወደሚኖርበትም ቦታ መራቻቸው። እነርሱም አንሥተው ተሸከሙት እየዘመሩና እያመሰገኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን አደረሱት በቤተ መቅደሱም ፊት ለፊት በወንበሩ ላይ አስቀመጡት ምእመናንም ሁሉ ወደርሱ እየመጡ ከእርሱ ይባረኩና የተቈረጡ ሕዋሳቱን ይሳለሙ ነበር።ንጉሥ ቂስጠንጢኖስም የከበሩ የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ኤጲስቆጶሳትን የአንድነት ጉባኤን በኒቅያ አገር በሰበሰበ ጊዜ ይህ የከበረ ቶማስ ከእሳቸው አንዱ ነው።

ንጉሡም ወደ እንርሱ ገብቶ ሰላምታ ሰጣቸውና ከእርሳቸውም ቡራኬ ተቀበለ። የዚህ የቅዱስ ቶማስን ተጋድሎውን በነገሩት ጊዜ ወደርሱ ቀርቦ ሰገደለት ሕዋሰቱም ከተቈረጡበት ላይ ተሳለመው አዝኖና እጅግም አድንቆ ሕዋሳቱን ዳሠሠው ፊቱንና ዐይኖቹን አሻሸው።ከሀዲ አርዮስንም ተከራክረው ከረቱ በኋላ አውግዘው ለይተው ከወገኖቹ ጋር ከቤተ ክርስቲያን አሳደዱት። ከዚህም በኋላ መንፈስ ቅዱስ እንደ አስተማራቸውና እንደመራቸው የሃይማኖትን ትምህርት በአንደበታቸው ተናገሩ ሕግና ሥርዓትን ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍርድንም ሠሩ።

ከዚህም በኋላ ቅዱስ ቶማስ ወደ መንበረ ሢመቱ ሔደ ካህናቱንና መንጋዎቹን ሁሉ ሰብስቦ አነበበላቸው እርሱንም እንዲአስተውሉት እንዲጠብቁትም በመጠበቅም እንዲጸኑ አዘዛቸው።ጥቂት ዘመናትም ከኖረ በኋላ በሰላም በፍቅር አረፈ የሹመቱም ዘመን አርባ ዓመት ነው በዚህም እግዚአብሔርን አገለገለው። ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ተጋዳይ አባት ጸሎት ይማረን ። በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

                   ፨፨፨

በዚችም ቀን ታላቅ የከበረ ሐዲስ ሐዋርያ የትሩፋትም መምህር የሆነ አባታችን ተክለ ሃይማኖት አረፈ። የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ጸጋ ዘአብ የእናቱ ስም እግዚእ ኀረያ ነው እሊህም ቅዱሳን ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ብርሃንን ላበሩ ካህናት ከወገኖቻቸው የሆኑ ናቸው። እግዚእ ኀረያም መካን ስለሆነች ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እያዘኑ ሲጸልዩ ኖሩ።በዚህም ነገር እያሉ የዳሞት ገዥ ሞተለሚን ሰይጣን አነሣሣው የሸዋን አውራጃዎች እስከ ጅማ እስከ ገዛ ድረስ።የሀገር መኳንንቶችም በየተራቸው ሚስቶቻቸውን ይሰጡታል።ከማረከውም ደም ግባት ያላቸውን ሴቶች ያገኘ እንደሆነ ቁባቶቹ ያደርጋቸዋል።

በዚያም ወራት ወደ ጽላልሽ ደርሶ ብዙ ክርስቲያኖችን ገደለ ከእርሳቸውም የሚበዙትን ማረከ ጸጋ ዘአብም ከግድያ ፍርሃት የተነሳ ሸሸ አንድ ወታደርም ተከተለው እርሱም ወደ ባሕር ተወርውሮ ገባ በእግዚአብሔርም ፈቃድ በባሕሩ ውስጥ ተሸሸገ።ሚስቱን እግዚእ ኀረያንም ወታደሮቹ ማረኳት ወደ ሞተለሚም አደረሷት በአያትም ጊዜ ውበቷንና ላህይዋን አደነቀ በልቡም እጅግ ደስ ብሎት ብዙ ሽልማትን ጌጥን ሰጥቷት በሽልማትና በጌጥ ሁሉ ሸለማት አስጌጣትም የጋብቻ ሥርዓትንም ማዘጋጀት ጀመረ ለሠርጉም እንዲሰበሰቡ ወደመኳንንቶቹ ሁሉ ላከ።

እግዚእሸ ኀረያም ይህን በሰማች ጊዜ ከአረሚ ጋር አንድ ከመሆን ያድናት ዘንድ በብዙ ልቅሶ ወደ እግዚአብሔር ጸሎትን አደረገች። ያን ጊዜም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በብርሃናዊ ክንፉ ተሸክሞ ከዳሞት አገር ወደ ምድረ ዞራሬ አድርሶ ወዲያውኑ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ በሴቶች መቆሚያ አቆማት።ባሏ ጸጋ ዘአብም ከማዕጠንት ጋራ በወጣ ጊዜ እንደተሸለመች ቁማ አያት አድንቆ በልቡ ይቺ ሴት ምንድን ናት ወደዚህስ ማን አመጣት አለ።የማዕጠንቱንም ሥራ ጨርሶ ወጣ በጠየቃትና በመረመራት ጊዜ እርሷ ሚስቱ እግዚእ ኀረያ እንደሆነች አገኛት እርሷም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እግዚአብሔር ያደረገላትን ነገረችው።

ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ በአንዲት ሌሊት ተገለጠላቸው የዜናው መሰማት በዓለሙ ሁሉ የሚደርስ የተባረከ ልጅ ይወልዱ ዘንድ እንዳላቸው ነገራቸው አበሠራቸው።ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ይህ ቅዱስ ተፀንሶ በታኀሣሥ ወር በሃያ አራት ተወለደ በጸጋ ዘአብና በእግዚእ ኀረያ ቤታቸው ታላቅ ደስታ ሆነ ከዘመዶቻቸውና ከጐረቤቶቻቸው ጋራ ደስ አላቸው።

ለክርስትና ጥምቀትም በአስገቡት ጊዜ ፍሥሓ ጽዮን ብለው ሰየሙት።ሕፃኑም አደገ ድንቅ ተአምራትንም እያደረገ ዕውቀትንና ኃይልንም ተመልቶ በመነፈስ ቅዱስ ጸና።ከዚህም በኋላ ዲቁና ይሾመው ዘንድ አባ ጌርሎስ ወደ ተባለ ጳጳስ ወሰዱት በዚያንም ዘመን በዛጔ መንግሥት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ብንያሚን ነበር።ወደ ጳጳሱም በአደረሱት ጊዜ ይህ ልጅ የተመረጠ ዕቃ ይሆናል ብሎ ትንቢት ተናገረለት።የዲቁና ሹመትንም ተቀብሎ ወደሀገሩ ተመለሰ ጐልማሳም በሆነ ጊዜ አራዊትን ሊአድን ወደ ዱር ሔደ።ቀትር ሲሆንም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልኩ የሚያምር ጐልማሳ አምሳል በቅዱስ ሚካኤል ክነፍ ላይ ተገለጠለትና እንዲህ አለው ወዳጄ  አትፍራ እንግዲህ የኃጢአተኞችን ነፍስ ወደ ሕይወት የምታጠምድ ትሆናለህ እንጂ አራዊትን የምታድን አትሆንም ስምህም ተክለ ሃይማኖት ይሁን እንደ ኤርምያስና እንደ አጥማቂው ዮሐንስ እኔ ከእናትህ ማኀፀን መርጬ አክብሬሃለሁና እነሆ በሽተኞችን ትፈውስ ዘንድ ሙታንንም ታሥነሣ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠሁህ ርከኵሳን አጋንንትንም ከሁሉ ቦታ ታሳድዳቸዋለህ።

ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ገንዘብን ሁሉ ለድኖችና ለምስኪኖች በተነ ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጠፋ ለሰው ምን ይጠቅመዋል  እያለ ቤቱን እንደ ተከፈተ ትቶ  ምርጒዙን ይዞ በሌሊት ወጣ።ከዚህም በኋላ ወደ ጳጳስ ሒዶ የቅስና ሹመት ተቀብሎ ለሸዋ አገር ሁሉ ወንጌልን መስበክ ጀመረ ዐሥራ ሁለት ሽህ ሦስት መቶ ነፍስ ያህል አጠመቀ ለጣፆት የሚሠውበትን ሁሉ ሻረ  በውስጡ የሚኖሩ አጋንንት እስከሸሹ ድረስ ዐፀዶቻቸውን ሁሉ ቆረጠ።

ሁለተኛም ወደ ዳሞት ምድር ሒዶ ብዙ ሟርተኞችንና አስማተኞችን ጠንቋዮችን አሳመነ ከሀዲ ሞተለሚም ብዙ ወራት ተቃወመው በጉማሬ ማጥመጃ ውስጥ በመጨመር ብዙ ጊዜ ወደ ገደል ወረወረው።  እርሱ ግን በደኀና ይመለሳል ደግሞ ሊወጋው ጦር ወረወረ ጦሩም ተመልሶ እጁን ወግቶ ተጠመጠመበት በተሠቃየም ጊዜ አባታችንን ለመነው እርሱም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አሳምኖ አዳነው የተጠመጠመበትንም ጦር ፈታለት ቀናውን መንገድ የሚያጣምሙ ሟርተኞችንም አጠፋቸው።

ከዚህም በኋላ በክብር ባለቤት ጌታችን ስም ያደረገውን ድንቅ ተአምራቱን አይተው የአገር ሰዎች ሁሉም ከንጉሣቸው ጋራ አመኑ የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶላቸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት አስተማራቸው በቀናች ሃይማኖትም አጸናቸው ከዚህም ሁሉ ጋራ በጾም በጸለት በስግደት ሁል ጊዜ  ያለ ማቋረጥ ተጠምዶ ይጋደል ነበር።ዜናውንም ሰምተው ወደርሱ የሚመጡትን የነፍሳቸውን ድኅነት ያስተምራቸዋል የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችን ኢየሱስን በማመን ያጸናቸዋል።

ከዚህ በኋላ በኤልያስ ሠረገላ ተቀምጦ ወደ አምሐራ ሀገር ሔደ ። በገድል ተጸምዶ ወደሚኖር መነኰስ ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል በአንዲት ቀን ደርሶ በዚያ እንደባሪያ ሲያገለግል ኖረ።  በአንድነት የሚኖሩ መነኰሳትንም  ያገለግላቸው ነበር የሞተውንም እስከማንሳት ድረስ ከደዌያቸው ይፈውሳቸው ነበር።በዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ከሆነው በኋላ ሐይቅ በሚባል ቦታ ወደሚኖር ወደ ኢየሱስ ሞዓ የእግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው ሔዶ ከእርሱም የምንኲስና ልብስ ቀሚስና ቅናትን ተቀበለ።ከዚያም ወደ ደብረ ዳሞ ሔዶ ለአቡነ አረጋዊ አራተኛ ከሆነ ከአባ ዮሐኒ ዘንድ ቆብንና አስኬማን ተቀበለ።ሁለተኛም ወደ ኢየሩሳሌም ሒዶ ከከበሩ ቦታዎችና ከሊቀ ጳጳሳቱ ቡራኬን ተቀበለ።

በዚያም ወደ ሸዋ ምድር ተመልሶ የአባቱ ወንድም ልጅ የሆነ አባ ዜና ማርቆስን አገኘው በወግዳ በረሀም በአንድነት ኖሩ።  ከዚያም ግራርያ ወደ ሚባል አገር ሒዶ በኮረብታ መካከል ዋሻ አዘጋጅቶ ተቀመጠ በቀንም በሌሊትም ከዚያ አይወጣም ነበረ ከጥቂት ቅጠልም በቀር እህልን አይቀምስም መጠጡም ጥቂት ውኃ ነው።ብዙ ወንዶችና ሴቶች ወደርሱ መጥተው መነኰሳቶች ሆኑ በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ መኝታ ላይ ተኝተው ያድራሉ እርስበርሳቸውም አይተዋወቁም እነርሱም እንደ ሕፃናት ናቸው በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜም በአንድነት ይቆማሉ በዘመኑ ሰይጣን ሰለ ታሠረ ወንዱ ሴቷን ሴት እነደሆነች አያውቅም እንዲሁም ሴቷ ወንዱን ወንድ እንደሆነ አታውቅም።

ከዚህም በኋላ መጠጊያ ሠርቶ በፊቱ በኋላው በቀኙ በግራው የተሳሉ ፍላጻዎችን ተከለ ይህንም ማድረጉ በመደገፍና በመተኛት እንዳያርፍ ነው በዚያም እግሩ ከቅልጥሙ እስቲሰበር ሰባት ዓመት ቆመ።በዚያም ወራት ምንም የዕንጨት ፍሬ ወይም ቅጠል ሳይቀምስ ውኃም ሳይጠጣ ኖረ።ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርቶስ ወደርሱ  መጣ  ከእርሱም ጋራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ የከበሩ ነቢያትና ሐዋርያት ሁሉም ሰማዕታትና ጻድቃን የጳጳሳት አለቆች የመላእክት አለቆችም ከሠራዊቶቻቸው ጋራ አሉ።መድኃኒታችንም እንዲህ አለው ወዳጄ ሆይ አንተ በመከራዬ መሰልከኝ እኔም በመንግሥቴ ከእኔ ጋራ እንድትመስለኝ አደርግሃለሁ። እነሆ የዚህ ዓለም ድካምህ ተፈጸመልህ በእኔ ዘንድም የምቀበለው ሆነ ከእንግዲህስ መንግሥተ ሰማያትን ትወርስ ዘንድ ና።

እነሆ ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ገድልህን ለሚጽፍ ለሚያነበውና ለሚሰማውም ቤተ ክርስቲያንህን ለሚሠራ በስምህ መባ ለሚሰጥ ለድኆችም በስምህ ለሚመጸውት በመታሰቢያህም ቀን ለሚቁርብ ስለ አንተ በጎ ሥራ ለሚሠራ ሁሉ እኔ እስከ ዐሥር ትውልድ እምርልሃለሁ።አባታችንም እጅግ ደስ አለው ለጌታችንም ሰገደ ጌታችንም ከእርሱ ዘንድ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ። ከዚህም በኋላ  አባታችን በንዳድ በሽታ ጥቂት ታመመ ዕድሜውም ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀን ሆኖት በለመለመ ዕርግና አረፈ።በመዘመርና በማመስገን አክብረው ገንዘው በዋሻው ውስጥ ቀበሩት።ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን ተክለ ሃይማኖት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
በዚችም ቀን ደግሞ, ኢትዮጵያዊት የሆነች ተጋዳይ የከበረች ክርስቶስ ሠምራ የዕረፍቷ መታሰቢያ ነው ዳግመኛ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብም መታሰቢያቸው ነው።በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። 

=>ነሐሴ 24 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (መምሕረ ትሩፋት)
2.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ (ጻድቅት)
3.ቅዱስ ቶማስ ዘመርዐስ
4.አበው አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ

=>ወርኀዊ በዓላት
1.አቡነ ዘዮሐንስ ጻድቅ ዘክብራን
2.ቅዱስ አጋቢጦስ (ጻድቅ)
3.ቅዱስ አብላርዮስ ታላቁ
4."24ቱ" ካኅናተ ሰማይ (ሱራፌል)
5.ቅዱስ አባ ሙሴ ጸሊም

=>+"+ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል:: ጻድቅን በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል:: +"+ (ማ 10፥ 41)


ወስብሐት ለእግዚአብሔር 
 ወለወላዲቱ ድንግል
 ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

0 comments:

Post a Comment

አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።