ነሐሴ 7 የእመቤታችን ፅንሰት
“ወይእዜኒ ኦ ውሉደ እግዚአብሔር ወማኅበረ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናስተብፅዖሙ ለሐና ወለኢያቄም ዘወለዱ ለነ ዛተ ቡርክተ ወቅድስተ መርዓተ፤ አይ ይእቲ ዕለት ዕለተ ሩካቤሆሙ ንጽሕት ...”(አኹንም የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆችና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማኅበሮች ሆይ ይኽቺን የተባረከችና የተመረጠች ሙሽራ የወለዱልንን ኢያቄምንና ሐናን እናመስግናቸው የማትነቀፍ የእስራኤል ድንግልን የተባረከችዋን ፍሬ ያፈራችበትን ንጽሕት የምትኾን የሩካቤያቸው ዕለት እንደምን ያለች ዕለት ናት? ከይሁዳ ወገን ለኾነችው ንጽሕት ርግብ መፀነስ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተደረገ የጾታዊ ተዋሕዷቸው ቀን ይኽቺ እንዴት ያለች የተመረጠች ቀን ናት፤ ለንጉሥ ማደሪያ አዳራሽ መመሥረት የተደረገባት (የኾነባት) የደስታ ቀን እንዴት ያላት ቀን ናት?)
ነሐሴ 7 የእመቤታችን የፅንሰትዋ ድንቅ ታሪክ
በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
✔❖ የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ጴጥሪቃ ቴክታ ሲባሉ “ወኮኑ ክልኤሆሙ ጻድቃን ወፈራህያነ እግዚአብሔር ወይትአመንዎ ለአምላኮሙ በጥቡዕ ልብ እንበለ ኑፋቄ” ይላል (ኹለቱም ሰዎች ደጋጐችና እግዚአብሔርን የሚፈሩ ያለምንም መጠራጠር በፍጹም ልቡናቸው በአምላካቸው የሚተማመኑ ነበሩ)፤ እነርሱም በጊዜው ይኽ ቀራችኊ የማይባሉ ባለጠጎች ነበሩ፤ ከሀብታቸው ብዛት የተነሣ ወርቁን ብሩን እንደ ዋንጫ እያሠሩ በላሙ በበሬው ቀንድ ላይ ይሰኩት ነበር፤ ይኽን ያኽል አቅርንተ ወርቅ፣ አቅርንተ ብሩር እየተባለ ይቈጠር ነበር፤ የዕንቊ ጽዋ እንኳ ፸፣ ፹ ያኽል ነበራቸው ይላል[1]፡፡
✔❖ ከዕለታት ባንዳቸው ጴጥሪቃ ወደ ቤተ መዛግብቱ ገብቶ የሀብቱን ብዛት አይቶ ሚስቱ ቴክታን “ለመኑ ዘዘገብነ መዛግብቲነ አልብነ ውሉድ ዘይወርሰነ አንቲኒ ወአነሂ መካን ንሕነ” (የሰበሰብነው ገንዘብ ስንኳን ለኛ ለልጅ ልጅ ይተርፍ ነበር አንቺም እኔም መካኖች ነንና የሚወርሰን ልጅ የለንም) በማለት ተናገራት፤ ርሷም እንዲኽ ማለቱ ወላድ የፈለገ መስሏት በሐዘን ኾና “አምላከ እስራኤል ከኔ ልጅ ባይሰጥኽ ከሌላ ይሰጥኽ ይኾናልና ሌላ አግብተኽ ውለድ” አለችው፤ ርሱም “አነሂ ኢይፈቅድ የአምር አምላከ እስራኤል ከመ ኢየሐስቦ ለልብየ” (ይኽንስ እንዳላደርገው በልቤም እንዳላስበው የእስራኤል አምላክ ያውቃል) በማለት ተናገረ፡፡
❖ ርሷም ዐዝና ሳለ ራእይ ታያለች፤ ነጭ እንቦሳ ከማሕፀኗ ስትወጣ እንቦሳዪቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ሰባት ስትደርስ ሰባተኛዋ ጨረቃን ስትወልድ፤ ጨረቃ ፀሓይን ስትወልድ አይታ በአድናቆት ለባሏ “ግሩም ግብሩ ለእግዚአብሔር ትማልም ርኢኩ በሕልምየ ጸዐዳ ጣዕዋ ወጽአት እምከርሥየ ይእቲኒ ወለደት ጸዐዳ ጣዕዋ እስከ ሰብዐቲሆን ወሳብዕታኒ ወለደት ወርኀ ወወርኅኒ ወለደት ፀሓየ” (የእግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነው፤ ትናንትና ማታ በሕልሜ ነጭ ጥጃ ከማሕፀኔ ስትወጣ ያችም ነጭ ጥጃ ደግሞ ነጭ ጥጃ ስትወልድ እንደዚኽ እየኾነ እስከ ሰባት ትውልድ ሲደርሱ ሰባተኛዪቷም ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃዋ ደግሞ ፀሓይን ስትወልድ አየኊ) በማለት አስረዳችው።

❖ ርሱም በእጅጉ ተደንቆ ሕልም ወደሚፈታ ሰው ዘንድ በመኼድ የሚስቱን ራእይ ነገረው፤ ያም ሕልም ተርጓሚ ምስጢር ተገልጾለት ሰባት አንስት ጥጆች መውለዳችኊ ሰባት ሴቶች ልጆች ይወለዳሉ፤ ነጭ መኾናቸው ደጋጎች ልጆች መኾናቸው ሲኾን “ወሳብእታኒ ትከብር እመላእክት ወትትሌዐል እምኲሉ ሰብእ ወበእንተ ፀሓይኒ ኢያእመርኩ” (ሰባተኛዪቱ ጨረቃን መውለዷ ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ናት፤ የፀሓይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም) በማለት ተረጐመለት፤ ርሱም ለሚስቱ ነገራት፤ ርሷም “የእስራኤል አምላክ የሚያደርገውን ርሱ ያውቃል” በማለት ፈጣሪዋን አመሰገነች፡፡
❖ ከዚያም ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች ስሟንም ሔሜን አሏት፤ ሔሜን → ዴርዴን ወለደች፤ ዴርዴም → ቶናን፤ ቶናም →ሲካርን ወለደች፤ ሲካርም→ ሴትናን፤ ሴትናም →ሔርሜላን ወለደች፤ ሔርሜላም የተከበረችና የተመረጠች ዓለሙን ኹሉ ለፈጠረ ጌታ አያት ለመኾን የበቃች ሐናን ወልዳለች፤ የዝማሬና የትንቢት ጸጋ ከእግዚአብሔር የተሰጡት ክቡር ዳዊት ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ክብር በተለይም ስለ ሥርወ ልደቷ አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት በመዝ ፹፮፥፩‐፯ ላይ “መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን” (መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ላይ ናቸው) በማለት የእመቤታችን ሥርወ ልደት ከቤተ መንግሥት ከቤተ ክህነት ከኾኑት ከተቀደሱት ከቅዱሱ ኢያቄምና ከቅድስቲቱ ሐና የመኾኑን ነገር በምሳሌ የገለጸው ሊፈጸም ሐና በመልካም አስተዳደግ አድጋ አካለ መጠን ስታደርስ ከነገደ ይሁዳ ከመንግሥት ወገን የተወለደ የቅስራ ልጅ የአልዓዛር የልጅ ልጅ ከሚኾን ከኢያቄም ጋራ አስተጫጭተው አጋቧት፡፡
✔❖ ዳዊት ብቻ ሳይኾን ቊጥሩ ከዐበይት ነቢያት መኻከል የኾነው ነቢዩ ኢሳይያስ ጥበብን በሚገልጽ ትንቢትን በሚያናግር በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ከነገደ ዕሴይ ወገን የምትወለድ ስለመኾኗና ከርሷም ጽጌ (አበባ) የተባለ አካላዊ ቃል ክርስቶስ እንደሚወለድ ተገልጾለት በምዕ ፲፩፥፩ ላይ "ትወፅእ በትር እምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ" (ከዕሴይ ሥር በትር ትወጣላች፤ አበባም ከርሷ ይወጣል) በማለት አስደናቂ ትንቢትን ተናግሮ ነበር፡፡

✔❖ ሐናና ኢያቄምንም “ወክልኤሆሙ ኄራን ወሥሙራን እሙንቱ ወየሐውሩ በሕገ እግዚአብሔር እስመ እግዚአብሔር ኀረዮሙ ወአፍቀሮሙ ትካት” ይላቸዋል እግዚአብሔርን የሚወድዱ በሕጉ የሚኖሩ ደጋጎችና አምላክም የመረጣቸው ሲኾኑ ሐና መካን በመኾኗ ምክንያት ኹለቱም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ዕለት ዕለት በመኼድ ለዐይናቸው ማረፊያ ለልባቸው ተስፋ የሚኾን ልጅ እንዲሰጣቸው ይለምኑ እንደነበር፤ "Protoevangelium of James" Protoevangelium of James”
(ፕሮቶቫንጊሊዩም ኦፍ ጀምስ) የሚለው ያዕቆብ የጻፈው ጥንታዊዉ መጽሐፍ በስፋት ይገልጻል[1]፡፡
✔❖ ከዕለታት ባንደኛው ሲያዝኑ ሲጸልዩ ውለው ሲመለሱ “ወርእዩ አርጋበ እንዘ ይትፌሥሑ ምስለ ውሉዶሙ” ይላል ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ደስ ብሏቸው ሲጫወቱ አይተው ሐና “አቤቱ ጌታዬ ግዕዛን ለሌላት እንስሳ ልጅ የሰጠኽ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ነሣኸኝ” ብላ ምርር ብላ አለቀሰች፤ ወዲያው ሱባዔ ይገባሉ፤ ኢያቄም ወደ በረሓ ኼዶ ሲጸልይ ሐና ደግሞ በቤቷ ዙሪያ ባለው የተክል ቦታ ሱባዔ ያዘች፤ በሱባዔያቸው ፍጻሜ ኹለቱም ራእይ አይተው ተነጋግረዋል፡፡
❖ “ይቤላ ኢያቄም ለሐና ብእሲቱ እንዘ ይትረኀዉ ሰብዐቱ ሰማያት ዖፍ ጸዐዳ መጽአ ኀቤየ ወነበረ ዲበ ርእስየ” ይላል ሰባቱ ሰማያት እንደ መጋረጃ ተገልጠው ከላይኛው ሰማይ ነጭ ዎፍ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየኊ ብሎ የተገለጸለትን ለሐና ነግሯታል፤ ይኸውም የራእዩ ምስጢር፡- ዎፍ የተባለው አካላዊ ቃል ክርስቶስ ሲኾን፤ ነጭነቱ ንጽሐ ባሕርዩ ነው፤ ከላይ ወርዶ በራሴ ላይ ሲቀመጥ አየኊ ማለቱ የኢያቄምን ባሕርይ ባሕርይ እንደሚያደርግ ሲያጠይቅ ሲኾን፤ ሰባቱ ሰማያት የተባሉ የጌታችን ምልአቱ፣ ስፍሐቱ፣ ርቀቱ፣ ልዕልናው፣ ዕበዩ ናቸው፡፡
❖ ሐናም ተገልጾላት “ትቤሎ ሐና ለኢያቄም ብእሲሃ አነኑ ርኢኩ በሕልምየ ርግብ ጸዐዳ መጽአት ኀቤየ ወነበረት ዲበ ርእስየ ወቦአት ውስተ እዝንየ ወኀደረት ውስተ ከርሥየ” ይላል ለባሏ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ በዦሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየኊ ብላዋለች፤ ይኽ የራእይ ምስጢር፡- ርግብ የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትኾን፤ ነጭነቷ ንጽሕናዋ፣ ቅድስናዋ፣ ዘላለማዊ ድንግልናዋ ነው፤ ነጭ ርግብ መጥታ በራሴ ላይ ተቀምጣ ከራሴ ላይ ወርዳ ወደ ዦሮዬ ገብታ በማሕፀኔ ስትተኛ አየኊ ማለቷ ብሥራተ ገብርኤልን በዦሮዋ ሰምታ በግብረ መንፈስ ቅዱስ አምላክን የምትፀንሰውን ንጽሕት ርግብ የተባለችውን እመቤታችንን የምትወልድ መኾኗን ሲያጠይቅ ነው፡፡
✔❖ ኢያቄምና ሐናም ይኽነን ራእይ ሐምሌ ፴ ቀን ካዩ በኋላ “ወንድ ልጅ ብንወልድ ወጥቶ ወርዶ ይርዳን አንልም ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ይኾናል፤ ሴትም ብንወልድ ለቤተ እግዚአብሔር መጋረጃ ፈትላ ትኑር” ብለው ስእለት ከተሳሉ በኋላ ራእይ አየን ብለው ዕለቱን አልተገናኙም፤ አዳምንና ሔዋንን “ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሏት” ብሎ የተናገረው አምላክ ለእኛም ይግለጽልን ብለው ዕለቱን አልጋ ምንጣፍ ለይተው እስከ ሰባት ቀን ድረስ እየብቻቸው ሰነበቱ፤ ነሐሴ በባተ በሰባተኛው ቀን “ከሰው የበለጠች ከመላእክት ኹሉ የከበረች ልጅ ትወልዳላችኊ" ብሎ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለሐና ነግሯት በፈቃደ እግዚአብሔር በብሥራተ መልአክ እመቤታችን ነሐሴ ሰባት እሑድ ተፀንሳለች፤ በእናቷ ማሕፀን ሳለችም “መንፈስ ቅዱስ ዐቀባ እምከርሠ እማ” እንዲል እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጥንተ አብሶ ባመጣው መርገም እንዳትያዝ ጠብቋታል፡፡
✔❖ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም መፀነስ ከሊቃውንት መኻከል አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ላይ
“ሚ ቡርክት ወቅድስት ይእቲ
ሰዓተ ትፍሥሕት ሐና ዘጸገየተኪ ባቲ
ወፈረየኪ ለሕይወት ኢያቄም መዋቲ
እሴብሕ ተአምረኪ ርግብየ አሐቲ
ወድኀኒተ ኲሉ ዓለም እስመ ኮንኪ አንቲ”
(ሐና አንቺን የፀነሰችባት የደስታ ቀን ምን ያኽል የተባረከች የተቀደሰች ናት፤ ሟች ኢያቄምም ለሕይወት አንቺን ያፈራባት ቀን ምን ያኽል የተባረከች የተቀደሰች ናት፤ አንዲቱ ርግቤ ማርያም አንቺ የዓለሙ ኹሉ መድኀኒት ኾነሻልና ታምርሽን አመሰግናለኊ)[1] በማለት ዓለምን ኹሉ በደሙ ፈሳሽነት ያዳነ ንጉሣችን፣ ፈጣሪያችን ክርስቶስን በድንቅ ተአምር ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ የወለደችልን ምክንያተ ድኂን ርግበ ሰሎሞን የተባለች የቅድስት ድንግልን የመፀነሷን ነገር በአድናቆት ገልጸዋል፡፡

✔❖ ታላቁ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በአርጋኖን መጽሐፉ ላይ የዜና ጽንሰቷን ነገር ሲገልጽ “ወይእዜኒ ኦ ውሉደ እግዚአብሔር ወማኅበረ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናስተብፅዖሙ ለሐና ወለኢያቄም ዘወለዱ ለነ ዛተ ቡርክተ ወቅድስተ መርዓተ፤ አይ ይእቲ ዕለት ዕለተ ሩካቤሆሙ ንጽሕት ...” (አኹንም የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆችና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማኅበሮች ሆይ ይኽቺን የተባረከችና የተመረጠች ሙሽራ የወለዱልንን ኢያቄምንና ሐናን እናመስግናቸው የማትነቀፍ የእስራኤል ድንግልን የተባረከችዋን ፍሬ ያፈራችበትን ንጽሕት የምትኾን የሩካቤያቸው ዕለት እንደምን ያለች ዕለት ናት? ከይሁዳ ወገን ለኾነችው ንጽሕት ርግብ መፀነስ በእግዚአብሔር ፈቃድ የተደረገ የጾታዊ ተዋሕዷቸው ቀን ይኽቺ እንዴት ያለች የተመረጠች ቀን ናት፤ ለንጉሥ ማደሪያ አዳራሽ መመሥረት የተደረገባት (የኾነባት) የደስታ ቀን እንዴት ያላት ቀን ናት?)[1] በማለት የፅንሰቷን ነገር አደነቀ።
❖ ሊቁ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴ ማርያም መጽሐፉ በቊ ፴፰ ላይ “ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ” (ድንግል ሆይ በኀጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለሽም በሕግ በኾነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ) በማለት ቅድስት ድንግል ማርያም ጥንተ ኀጢአት ካመጣው መርገም በፅንሰቷ ጊዜ እንዳትያዝ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የተጠበቀ መኾኑን ተናግሯል፡፡❖ “ወእምድኅረ ስድስቱ አውራኅ ተዐውቀ ፅንሳ ለሐና” ይላል፤ ከስድስት ወርም በኋላ የሐና ፅንሷ እየታወቀ ሲመጣ ጎረቤቶቿ መፅነሷን ይረዱ ዘንድ በአድናቆት ማሕፀኗን ይዳስሱ ነበር፤ በተለይም ዐይኗ የታወረ የሐና ዘመዷ የአርሳባን ልጅ የምትኾን አንዲት ሴት የሐናን ማሕፀን ዳስሳ ዐይኗን ብትነካው በርቶላት በታላቅ ደስታ ኾና “ብፅዓን ለኪ ኦ ሐና እስመ እም ፍጥረተ ዓለም አልቦ ዘከማኪ ዘይፌውስ በከርሡ አዕይንተ ዕውራን” (ሐና ሆይ ብፅዓን ይገባሻል ዓለም ከተፈጠረ ዠምሮ እንዳንቺ በማሕፀኑ የዕውራንን ዐይን የሚያበራ የለምና) በማለት አመስግናታለች፤ ከዚኽ በኋላ ዝናዋ በሀገሩ ኹሉ ተሰምቶ ሕሙማን ኹሉ ማሕፀኗን እየዳሰሱ ይፈወሱ ነበር፡፡
❖ አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም ዘደብረ ሐንታ በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው ላይ ይኽነን ሲገልጹ
“ጸግይየ ሣዕረ ዘኪሩቤል ልሳነ
ተአምረኪ በነጊር እመ ኢፈጸምኩ አነ
ባሕቱ አአኲት ማርያም ዘጾረተኪ ማሕፀነ
እንዘ ሀለወት ፀኒሳ ኪያኪ ርጢነ
ለለገሰስዋ ላቲ ትፌውስ ዱያነ”
(ሳርን የኾንኊ እኔ የኪሩቤል አንደበትን ገንዘብ አድርጌ ታምርሽን በመንገር በማስተማር ባልፈጽምም ነገር ግን ማርያም የተሸከመቺሽን ማሕፀን አመሰግናለኊ፤ መድኀኒት አንቺን ፀንሳ ሳለች ርሷን የዳሰሷትን ድዉያንን ኹሉ ትፈውስ ነበር)[1] በማለት እመ መድኅነ ዓለም ገና ሳትወለድ የተሠራውን ድንቅ ተአምር አመስግነዋል፡፡

❖ ይኽ የቅድስት ድንግል ማርያም የፅንሰት በዓል በመላው ዓለም የሚታወቅ ሲኾን ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊት የኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የአምላክ እናት የተፀነሰችበት ይኽነን በዓል ነሐሴ ፯ ቀን በታላቅ ድምቀት በማሕሌት፣ በቅዳሴ የምታስበው ሲኾን በዓሉም “ፅንሰታ ለማርያም” በመባል ይታወቃል፤ በዓለም ላይ ያሉ ክርስቲያኖች ደግሞ በዓሉን “The conception of the Theotokos” (የአምላክ እናት መፀነስ) በማለት ሲያከብሩት ወሩን ግን የልደት በዓልን ለማክበር በሚዘጋጁበት በታኅሣሥ አድርገው በ፱ኛው ቀን “December 9” ላይ ያስቡታል[1]፡፡
የአምላካችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ እኛ ልጆችሽን አብዝተሽ ባርኪን፨
ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
የአምላካችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ እኛ ልጆችሽን አብዝተሽ ባርኪን፨
ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
0 comments:
Post a Comment
አስተያየት ወይም መልዕክት ካልዎት፤ ከዚህ በታች ያለውን ሰሌዳ ይጠቀሙ።